በአማራ ክልል በሁለት ወራት ብቻ 200 በላይ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ተፈጸመባቸው
በአዲሱ ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ወራት ፤ መስከረምና ጥቅምት ብቻ በአማራ ክልል ከ200 በላይ ሴቶች የአስገድዶ መድፈር ጥቃት እንደደረሰባቸው ተገለጸ፡፡
የክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለሆርን ፍሪኩዌንሲ እንደገለጸው ሴቶች በመንግስት የጸጥታ ኃይላት ጨምሮ በክልሉ መሳሪያ ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ቡድኖች አስገድዶ መደፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ውትወታዎች አማካኝነት ቀንሶ የነበረው የጎጂ ባህላዊ ድርጊቶች መጨመራቸው እና ከዚህም ጋር ተያይዞ ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን እንዲገረዙ እያደረጉ መሆኑን ከቢሮው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት በክልሉ የጸጥታ ችግር ባለባቸው እና በሌሎችም አካባቢዎች አሁንም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን፣ በክልሉ ሴቶች፣ ሕፃናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ባልደረባ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሙያ አስታውቀዋል። ባለሙያው እንዳሉት፣ በክልሉ በሴቶች ላይ የጾታዊ ጥቃት ብቻ ሳይሆን የሞራልና የኢኮኖሚ ጥቃትም እየደረሰባቸው ይገኛል ነው ያሉት።
በተጨማሪም፣ በክልሉ የጸጥታ ችግር ሳቢያ በርካታ ሴቶች ለወሲብ ንግድ ተጋልጠዋል ብለዋል፡፡ በክልሉ በመንግስት እና በፋኖ ሃይሎች መካከል በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሴቶች በእጅጉ ተጎጂ እየሆኑ ነው ተብሏል፡፡ በተለይ ትምህርት በተጀመረባቸው አካባቢዎች ለትምህርት የሚሄዱ ሴት ልጃገረዶች በየመንገዱ እየተደፈሩ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የዚህ ሁሉ ጥቃት መነሻ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ መቃወስ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ባለሙያው፤ የጸጥታው መደፍረስ በሴቶች ላይ ለሚደርሰው ጥቃት አባባሽ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል። ችግሩ አሁን ካለበት ደረጃ እንዳይባባስ ለመከላከል፣ ቢሮው ከሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል አካላት ጋር በመተባበር ግብረ ኃይል አቋቁሞ እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

