በመተከል በተፈጸመ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች ተገደሉ
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉራ ወረዳ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ30 በላይ ሰላማዊ ሰዎችመገደላቸውን ነዋሪዎች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ተናግረዋል።
ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት ግንቦት 4/2018 መነሻቸው አሶሳ አድርገው ወደ መተከል ግልገል በለስ ከተማ፣ በአውቶቡስሲጓዙ በነበሩ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ነው። ሦስት የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች ተከታትለው እየተጓዙ ባለበት አጋጣሚ፣መንገድ ላይ ባደፈጡ ታጣቂዎች የተኩስ እሩምታ እንደተከፈተባቸው እና ተጓዦች ለጉዳት እንደተዳረጉ ለማወቅ ተችሏል።
ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቁት በአውቶቡሶቹ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውንተናግረዋል። ከሟቾቹ በተጨማሪ 50 ገደማ ተሳፋሪዎች በጥይት ከደረሰባቸው ጥቃተ የተነሳ ከከባድ እስከ ቀላላ የአካልጉዳት አስተናግደዋል። ከጥቃቱ የተረፉ ከ10 በላይ ሰዎች ደግሞ ታፍነው መወሰዳቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። በጥቃትፈጻሚዎቹ ታጣቂዎች ታፍነው የተወሰዱት ከተከፈባቸው የተኩስ እሩምታ፣ ተርፈው ያልቆሰሉ ናቸው ተብሏል።
የጥቃቱ ፈጻሚዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንደ አዲስ እየተደራጁ ያሉት የጉምዝ ታጣቂዎች መሆናቸውንም ምንጮች አያይዘው ገልጸዋል።
ታጣቂ ቡድኑ ከመንግሥት ጋር ተደራድሮ ወደ ሰላማዊ ፓርቲነት ከተመለሰው፣ የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ(ጉህዴን) የተገነጠለ ሲሆን፤ የፓርቲው አመራሮች እንደ አዲስ መተከል ውስጥ ጥቃት እየፈጸመ የሚገኘው የታጠቀ ቡድን በስማቸው ቢንቀሳቀስም እንደማይወክላቸው እየገለጹ ነው።


