በጂንካ የተከሰተው በሽታ ምንነት ተረጋግጧል
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጂንካ አካባቢ የተከሰተው በሽታ ማርበርግ ቫይረስ (marburg virus) መሆኑን ጤና ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታውቀዋል።
ሁለት የጤና ባለሙያዎችን ጨምሮ ስድስት ሰዎችን ለሞት የዳረገው በሽታ ማርበርግ ቫይረስ (Marburg Virus) መሆኑን በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሄራዊ ሪፈረንስ ላብራቶሪ በተሰራው የዘረመል ምርመራ መታወቁ ተገልጿል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘዉ ቫይረስ በሌሎች ምስራቅ አፍሪካ አገራት ከዚህ በፊት ከተከሰቱት ጋር ተመሳሳይ ዝርያ ያለዉ መሆኑ በዘረመል ምርመራው ተለይቷል።
ዛሬ ህዳር 5/2018 ዓ.ም አዲስ የበሽታውን ምልክት ያሳየ ወይም በቫይረሱ የተጠረጠረ ሰው አልተገኘም ተብሏል። ከቫይረሱ መገኘት ጋር ተያይዞ በጂንካ አካባቢ ፈጣን ምላሽ ሰጭ ቡድን ተሰማርቶ፣ በሽታዉን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር እየተሰራ ይገኛል። ፈጣን ምላሽ ሰጪ ቡድኑ የማኅበረሰብ አቀፍ የቅኝት ስራዎች፣ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ለይቶ ማከም፣ የማኅበረሰብ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እና ከተጠረጠሩ ሰዎች ጋር ንከኪ ያላቸዉን ሰዎች የመለየት ስራዎችን ያከናውናል።
እንዲሁም በአገር አቀፍ እና በክልል ደረጃ የሕብረተሰብ ጤና አደጋዎች የከስተት አስተዳደር ስርዓት ተቋቁሞ የፈጣን ምላሽ ስራዎችን በማስተባበር ላይ ይገኛል ተብሏል።
የቫይረሱ ምልክቶች በአፍ አፍንጫ እና ሌሎች የሰውነት ክፍሎች መድማት፣ ትኩሳት፣ ተቅማጥ እና ማስመለስ መሆናቸው ተጠቁሟል።
ማንኛውም የቫይረሱ ምልክቶች የታዩበት ሰው ወደ ህከምና ተቋማት መሄድና በወቅቱ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ እንደሚጠበቅ ተቋማቱ አሳስበዋል። የበሽታውን ተላላፊነት ለመከላከል ምልክት ከታየበት ማንኛዉም ሰው ጋር ንከኪ አለማድረግና የመከላከያ ዘዴዎችን መጠቀም ይመከራል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተከሰተውን ቫይረስ ተከትሎ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የዓለም የጤና ድርጅት 300 ሺ የአሚሪካ ዶላር በጀት መመደቡ የሚታወስ ነው፡፡

