በራያ አካባቢዎች ተሰማርቶ የነበረው ኮማንድ ፖስት አካባቢውን ለቆ ወጣ
ፎቶ ፋይል
የፌደራል መንግሥት በአወዛጋቢው የራያ አካባቢ ያሰማራው ኮማንድፖስት አካባቢውን ለቆ መውጣቱን ነዋሪዎች ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ተናገሩ፡፡
እንደ አላማጣና ኮረም ባሉ የራያ አካባቢዎች ተሰማርቶ የነበረው የመከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ ኮማንድ ፖስት ጥር 20/2018 ሌሊት ለቆ መውጣቱን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰው መረጃ ያመላክታል ፡፡ ኮማንድ ፖስቱ ከራያ አካባቢዎች ለቆ የወጣው ከሌሊቱ 8፡00 ገደማ መሆኑን ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን፣ ዛሬ ጥር 21/2018 ራያ ቆቦ መግባቱን ጠቁመዋል፡፡
ኮማንድ ፖስቱ በሌሊት ለቆ እንደወጣ የህወሓት ታጣቂዎች እንቅስቃሴያቸውን በከፍተኛ ደረጃ ያጠናከሩ ሲሆን፤ ኮማንድ ፖስቱ እና የህወሓት ታጣቂዎች ጎል ለጎን እየተንቀሳቀሱ የቆዩ ቢሆንም፤ አሁን ላይ በተፈጠረው የጦርነት ስጋት የፌደራል ኃይሎች አከባቢውን ለቀው በመውጣታቸው የሕወሓት ኃይሎች በስፋት መንቀሳቀስ መጀመራቸው ታውቋል።
በመከላከያ ሠራዊት እና ፌደራል ፖሊስ ጥምር ኃይል የተደራጀው ኮማንድ ፖስት ለቆ መውጣቱን ተከትሎ፣ የህወሓት ታጣቂዎች በማኅበረሰቡ ላይ ወከባ እየፈጠሩ ነው ተብሏል፡፡ ኮማንድ ፖስቱ በድንገት በመውጣቱ የማንነትና ወሰን ጥያቄ በማቀንቀን የሚታቁ የማኅበረሰብ መሪዎች ጭምር መታሰራቸው ተገልጿል፡፡
ቀድሞውኑ በህወሓት ኃይሎች የሚደርስባቸውን ወከባ በመፍራት ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በራያ ቆቦ የሚኖሩ የማኅበሰብ መሪዎች የነበሩ ቢሆንም፣ ኮማንድ ፖስቱ እንደወጣ በርካታ ሰዎች እየታሰሩ ነው ተብሏል፡፡ የህወሓት ታጣቂዎች እስርና ወከባ መጠናከሩን ተከትሎ፣ ስጋት ያለባቸውን ሰዎች ባገኙት አጋጣሚ ወደ ራያ ቆቦ እየወጡ መሆኑን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ኮማንድ ፖስቱ ከራያ አካባቢዎች የወጣው በጠለምት በኩል የተቀሰቀሰው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ ነው፡፡ ከሦስት ቀን በፊት የተቀሰቀሰው የጠለምት ግጭት ዛሬም መቀጠሉ የታወቀ ሲሆን፣ ውጥረቱ በሌሎች የትግራይ፣ አማራ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎችም ተባብሷል፡፡ የግጭቱ አውድ እየሰፋ መቀጠሉን ተከትሎ በተፈጠው ውጥረት ሊሆን እንደሚችል በተገመተው ምክንያት ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች ተሰርዘዋል፡፡ በዛሬው ዕለት ወደ ትግራይ በረራ የነበራቸው ሰዎች ጉዟቸው መሰረዙን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ መልዕክት እንደደረሳቸው ሰምነተናል፡፡


