በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ የፋኖ ኃይሎች ከ80 በላይ የከተማ ፖሊስና ሚሊሻ መግደላቸውን አስታወቁ
የከተማዋ አስተዳደር ድርጊቱን አምኗል።
በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ፣ በወረዳዋ ዋና ከተማ እስቴ መካነ ኢየሱስ፣ ጥቅምት 9 ቀን 2018 ዓ.ም ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ፣ የፋኖ ኃይሎች ሚሊሻና የከተማ ፖሊሶች መሽገውበት ወደነበረው ቦታ በድንገት በመግባት ከ80 እስከ 120 የሚሆኑ ሚሊሻዎችንና የከተማ ፖሊሶችን መግደላቸውን አስታውቀዋል።
የከተማዋ አስተዳደር በበኩሉ የሟቾችን ቁጥር በይፋ መናገር ባይፈልግም፣ ግድያው መፈጸሙን ግን አምኗል።
ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ፣ በእስቴ ከተማ አስተዳደር አንድ የሥራ ኃላፊ፤ በዞኑ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ የፋኖ ኃይሎች ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ ድንገተኛ ተኩስ በመክፈት በርካታ የሚሊሻ አባላትን መግደላቸውን ለሆርን ፍሪኩዌንሲ ተናግረዋል ። የሚሊሻና የፖሊስ አባላቱ የከተማዋን ደኅንነት በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሲያደርጉ እንደነበር ገልፀው፤ ታጣቂዎቹ ሌሊት በተኙበት መጥተው ድንገት ከበባ በማድረግ የተወሰኑ የሚሊሻና የፖሊስ አባላትን ገድለዋቸዋል ብለዋል።
ነዋሪዎች በበኩላቸው የፋኖ ታጣቂዎች በፈጸሙት የማጥቃት ዘመጃ 120 በላይ የሚሆኑ የጸጥታ አካላት ሥርዓተ ቀብር መፈጸሙን ለሆርን ፍሪኩዌንሲ አረጋግጠዋል።
ጥቃቱ ሲፈጸም የመከላከያ ሠራዊት አባላት በአካባቢው እንዳልነበሩ ከስፍራው ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ የሞቱት ሚሊሻና የፖሊስ አባላትም የገዳዮቹ የፋኖ አባላት ቤተሰቦች ናቸው ብለዋል። ከአንድ ቤተሰብ ሁለት ወይም ሦስት ልጅ ለትግል እንደሚወጣ የገለፁት ኃላፊው፤ አንደኛው ልጅ የፋኖ ታጣቂን ሲቀላቀል ሌላኛው ደግሞ ሚሊሻ ወይም ፖሊስ እንደሚሆን ተናግረዋል። የዛሬን መሰል ግጭት ሲፈጠር የሚገድለውም ሆነ የሚያቆስለው የራሱን ወንድም መሆኑ ደግሞ ይበልጥ ያሳዝናል ሲሉም ገልጸዋል። ለምሳሌም፣ ፋኖ የገባው አንድ ወጣት ሚሊሻ ሆኖ የከተማዋን ሰላም እያስጠበቀ የነበረውን ታላቅ ወንድሙን ገድሎት ተሰውሯል ነው ያሉት። ሟቹም ገዳዩም እርስ በርሱ መሆኑ ችግሩን እጅግ አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል።
በከተማዋ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ ፀጥታዋ አስተማማኝ እየሆነ ከመምጣቱ አንፃር ለሁለት ዓመት ተቋርጦ የቆየው ትምህርትም ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ በተፈጠረው ችግር ምክንያት ትምህርቱ መቋረጡንም የስራ ኃላፊው ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል። የትምህርት አገልግሎት በዋና ከተማዋ እስቴ መካነ ኢየሱስ መሰጠት ከጀመረ ጥቂት ቀናት የተቆጠሩ መሆኑንና ያንንም ተከትሎ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጀምሮ የነበረ ቢሆንም፣ በየዕለቱ የሚፈጠረው የፀጥታ ችግር ትልቅ ተግዳሮት ሆኖብናል ብለዋል። የፋኖ ኃይሎች በብዛት የሚንቀሳቀሱት በደቡብ ጎንደር ዞን ሥር በሚገኙ ወረዳዎች በመሆኑ፣ መንግሥትም በትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ አመላክተዋል። በአማራ ክልል በመንግሥትና በፋኖ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ባለው ውጊያ (ግጭት) የንፁኃን ሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ዝግ ሆነው ቀጥለዋል።

