ኮሎኔል ፈንታው ሙሃቤ የሚመራው የፋኖ ኃይል ከመንግስት ጋር በመደራደር ትግል ማቆሙን አስታወቋል
ላለፉት ሶስት ዓመታት በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች ነፍጥ አንስተው ከመንግስት ጋር ሲዋጉ ከነበሩ የፋኖ ኃይሎች ውስጥ በወሎ አካባቢ የሚንቀሳቀሰውን ከፊል ኃይል ሲመሩ የነበሩት ኮሎኔል ፈንታው ሙሃቤ ከክልሉ መንግስት ጋር ድርድር በማድረግ ጦራቸውን ይዘው መግባታቸው ታውቋል።
የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ወታደራዊ ምክትል አዛዥ እና በድርጅቱ አደረጃጀት ውስጥ የወሎ ጠቅላይ ግዛት ዕዝ ዋና አዛዥ የነበሩት ፈንታው በዛሬው ዕለት አቀባበል ሲደረግላቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ለሰላም የተከፈተው በር ለክልሉ ህዝብ ዘላቂ እፎይታን እንደሚሰጥ ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል።
የአማራ ክልል መንግስት በበኩሉ በክልሉ የሚስተዋሉ ማንኛቸውም ችግሮችን በሰላማዊ መንገድና በውይይት ለመፍታት በሩ ምንጊዜም ክፍት መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። በሰላም ስምምነቱ መዘግየት ምክንያት የከረረው የህዝቡ ቁስል እንዲህ ባሉ ድፍረት የተሞላባቸው የሰላም ጅማሮዎች ይሻራል ተብሎ የሚታመን ሲሆን፣ ሌሎች ታጣቂዎችም የህዝቡን ስቃይ በማየት የሰላም አማራጩን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቧል። የዛሬው ታሪካዊ እርምጃ ሰላም ባለመኖሩ ምክንያት የቆሙ የልማት ስራዎች እንዲቀጥሉና የዜጎች ስቃይ እንዲያበቃ እንደ ትልቅ ድል ተወስዷል ነው የተባለው። በቀጣይም የሰራዊቱ አባላት ወደ ተለያዩ የማቋቋሚያ ማዕከላት ገብተው ወደ መደበኛ ህይወታቸው የሚመለሱበት እና አካባቢው ወደ ቀድሞ ሰላሙ የሚመለስበት ስራ በቅንጅት እንደሚከናወን ታውቋል።
ይሁን እንጂ የኮሎኔል ፈንታው በድርድር መግባት ከመሰማቱ አስቀድሞ የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት አመራሩን ማገዱን በይፋዊ መግለጫ አስታውቆ ነበር።
ክዚህ ቀደም በካፒቴን ማስረሻ ሰጤ የሚመራው ኃይልም ከክልሉ መንግስት ጋር ድርድር በማድረግ እና የሰላም ስምምነት በመፈረም ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሱ የሚታወስ ነው።


