ቴዲ አፍሮ የአካላዊ ጥቃት ስጋት ውስጥ መግባቱ ተገለጸ
ጉዳዩን የዲፕሎማት ማኅበረሰብ በንቃት እየተከታተለው ነው
ተወዳጁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) በቅርቡ ለህዝብ ያደረሰውን እና 18 ሙዚቃዎች የተካተቱበት ኢቶሪካ አልበም ተከትሎ በርካታ እንግልቶች ሲደርሱበት እንደነበር እና አሁንም እሱን ጨምሮ በዙሪያው ያሉ ሰዎች ከመንግስት በኩል ከፍተኛ በደል እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ይታወቃል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የቅርብ ወዳጁ የኑስ የሱፍ እና የድምጻዊው ቃል አቀባይ ማህሌት ሰለሞን ሰብዓዊ መብታቸውን በሚጥስ መልኩ በመንግስት የጸጥታ አካላት መወሰዳቸው የሚታወስ ነው። እነዚሁ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ሰዓት ጀምሮ ወደ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ሲሆን በቁጥጥር ስር የዋሉብት ምክንያትም እንዳልተነገራቸው ለዝግጅት ክፍላችን የደረሱት መረጃዎች ያሳያሉ።
ወዳጁ የኑስ እና ባልደረባው ማህሌት በቁጥጥር ስር በዋሉብት ወቅት በዚያው ዕለት አመሻሽ ላይ የጸጥታ ኃይሎች ወደቴዲ መኖሪያ ቤት አቅንተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።
በአሁኑ ሰዓት ለሆርን ፍሪኩዌንሲ የደረሱ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አርቲስቱ በህግ ቁጥጥር ስር ይውላል ተብሎ ከሚጠበቀው በተቃራኒ ከባድ አካላዊ ጥቃት ሊደርስበት እንደሚችል ነው እየተጠበቀ የሚገኘው። ይህ ደግሞ በህግ አካላት ብቻ ሳይሆን ከመንግስት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው በሚባሉ ቡድኖች ኢመደበኛ አካላት ሊሆን እንደሚችል ታወቋል።
ከመንግሥት አካላት በገጠመው ወከባ እስከ አካላዊ ጥቃት የዘለቀ የደህንነት ስጋት ውስጥ መግባቱን የጠቀሱት የሆርንፍሪኩዌንሲ ምንጮች፤ ይህንንም ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም በመንግስት የደኅንነት አካላት መኖሪያ ቤቱ እና አካባቢው በመጠበቁ አርቲስቱ የእንቅስቃሴ ገደብ እንደገጠመው ታወቋል። ሌሎች ወዳጆቹም ወደ ቤቱ ሄደው መጠየቅ እንደኢሁም በስልክም ለማግኘት እንደተቸገሩ ለማወቅ ትቸሏል። ከቴዎድሮስ በተጨማሪ ሌሎች የስራ ባልደረቦቹ ዋና ማናጀሩ ጌታቸው ማንጉዳይን ጨምሮ ሁሉም እንቀስቃሴያቸው ብቻ ሳይሆን ስልኮቻቸውም ከእነሱ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነ የመረጃ ምንጮች አስታውቀዋል።
የመንግሥት የጸጥታ አካላት በቴዲ እና በዙሪያው ባሉ ሰዎች ላይ እያደረሱ ያሉትን ወከባ፣ መቀመጫቸውን አዲስ አበባያደረጉ የዲፕሎማት ማኅበረሰብ አካላት ጉዳዩን በንቃት እየተከታተሉት መሆኑን ዝግጅት ክፍላችን ሰምቷል።
የተወሰኑ ተፅዕኖ ፈጣሪ ሀገራት ኤምባሲዎች ሁኔታውን ከመከታተል ባሻገር፣ በጋራ እየተነጋገሩበት ነው። በቴዲ እና የቅርብሰዎቹ ላይ የሚደርሰው ጫና ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ፣ ኤምባሲዎች በይፋ አቋማቸውን ሊገልጹ እንደሚችሉ የዲፕሎማትምንጮች ጠቁመዋል። በቀጣይም ደግሞ ከመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጋር በቅርበት ለመነጋገርም አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ ኢምባሲዎች በተጨማሪም በአሜሪካ የሚገኙ 16 የማኅበረሰብ ድርጅቶች በአሜሪካ የኢትዮጵያ የህዝብ ጉዳዮች ኮሚቴ (AEPAC) አስተባባሪነት በድምጻዊው ላይ የሚደረሰውን ጉዳይ አስመልክተው ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሰሪያ ቤት ደብዳቤ ያስገቡ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ አዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኢምባሲ ጉዳዩን በአንክሮ እየተከታተለው እንደሚገኝ ምንጮች ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል።


