በባህር ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ የነበሩ ወጣቶች ህይወት አለፈ
ፎቶ ፋይል
ከየመን ወደ ጂቡቲ በባህር ሲጓዙ የነበሩ ኢትዮጵያን ወጣቶች ጀልባ ተገልብጦ መሞታቸውን ሆርን ፍሪኩዌንሲ ከቤተሰቦቻቸውና ባልደረቦቻቸው ሰምቷል።
መነሻቸውን ሳዑዲ አረቢያ ያደረጉት ኢትዮጵያን ወጣቶች በባህር ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ፣ ቀይ ባህር ላይ የጀልባ መገልበጥ አደጋ አጋጥሟቸዋል። ኢትዮጵያንን ጨምሮ በግምት 150 ይሆናሉ የተባሉ የአፍሪካ ስደተኞችን የጫነችው ጀልባ በአደገኛ የባህር ሞገድ ተመታ መገልበጧ ታውቋል።
በየመን ባህር ዳርቻ አቅራቢያ በደረሰው የጀልባ መገልበጥ አደጋው ቢያንስ 10 ኢትዮጵያን መሞታቸው ተገልጿል። አብዛኛዎቹ ተጓዦች ኢትዮጵያን እንደሆኑ ከተገመቱት መካከል የቅርብ ጓደኛዋ መሞቱን መስማቷን አንዲት ነዋሪነቷን ሳዑዲ አረቢያ ያደረገች ወጣት ለሆርን ፍሪኩዌሲ ተናግራለች።
ወጣቷ እንደምትለው በባህር ሲጓዝ የሞተው ጓደኛዋ በሕገወጥ መንገድ ሳዑዲ አረቢያ ይኖር የነበረ ወጣት ነው። በባህር ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሰ የነበረውም ሳውዲ አረቢያ በሕጋዊ መንገድ መኖር የሚችልበትን ሂደት ለማስፈጸም እንደነበር ጠቁማለች።
ወጣቷ “የልቤ ሰው መካሪዬ ወረቀት ላውጣ ብሎ በየመን ሄደ፣ ሆዴ እየፈራ በሰላም ተመልስ ብዬው፣ ይሄ ባህር በላው” በማለት እንባ እየተናነቃት ሁኔታውን አስረድታለች። ከጓደኛዋ ጋር በባህር እየተጓዙ የነበሩት አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያን በሕገወጥ መንገድ ሳዑዲ ሥራ ላይ የነበሩ ስደተኞች መሆናቸው ተናግራለች።
በደረሰው የጀልባ መገልበጥ አደጋ የተሳፈሩት አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያን መሆናቸውን ከየመን የባህር ጠረፍ አዘዋዋሪዎች መስማቷን ጠቁማለች። ወጣቷ እንደምትለው የቅርብ ጎደኛዋን ጨምሮ ከ10 ያላነሱ ኢትዮጵያን ስደተኞች መሞታቸውን አዘዋዋሪዎቹ ነግረዋታል።
ከአደጋው የተረፉ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ ስደተኞች ወደ የመን ባህር ጠረፍ ዳርቻ እንደደረሱም አዘዋዋሪዎቹ ገልጸዋ ተብሏል። በጀልባ መገልበጥ አደጋው ምን ያክል ሰዎች እንደሞቱና በህይወት እንደተረፉ በግልጽ እንዳልነገሯት ጠቁማለች።
አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊ በባህር ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱት በሕገወጥ መንገድ ከተሰደዱ በኋላ፣ የመኖሪያ ፈቃድ ወረቀት ለማግኘት ነው ተብሏል። በርካታ ኢትዮጵያ በሳዑዲ ራሳቸው ተደብቀው በሕገወጥ መንገድ የሚኖሩ ቢሆንም፣ በነጻነት የሚፈልጉትን ሥራ ለመሥራት የመኖሪያ ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።
ለዚህ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በሕጋዊ መንገድ ወረቀት አውጥተው ዳግም ወደ ሳዑዲ ለመመለስ ጥረት ያደርጋሉ። በዚህም በህይወታቸው ተወራርደው መጀመሪያ በባህር ወደ ኢትዮጵያ መመለስን ምርጫቸው ያደርጋሉ።
በሌላ በኩል ወደሀገራቸው የመመለስ ፍላጎት ያላቸው ሕገወጥ ስደተኞች ራሳቸው ለሳዑዲ መንግሥት አጋልጠው ይሰጣሉ። በሳውዲ ራስን አሳልፎ መሰጠት ለእስርና እንግልት የሚያጋልጥ ቢሆንም፣ ዓመታት ጥበቃ በኋላ በህይወት ወደ ሀገራቸው የመመለስ ዕድል ያገኛሉ።
ባለፈው አንድ ዓመት በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያን ስደተኞች ከሳዑዲ ተመልሰዋል። ምንም እንኳን በርካቶች ወደ ሀገራቸው እየተመለሱ ቢሆንም፣ አሁንም ከፍተኛ መጠን ያለው ወጣት በሕገወጥ መንገድ ወደ ስደት መጉረፉን ቀጥሏል።
መቆሚያ ባጣው ስደት ከጂቡቲ እሰከ የመን ባህር ጠረፍ የኢትዮጵያን ወጣቶች ህይወት በየጊዜው እየተገበረ ነው። በሀገራቸው የሰላም እጦትና የሥራ ዕድል መጥፉት ህይወት መግፋት የተሳናቸው ወጣቶች፣ ከፊት ለፊታቸው ሞት እንዳለ እያወቁ እንኳን ዛሬም ከመጓዝ አልቦዘኑም።
አሁን አሁን ደግሞ ገና ጉልበታቸው ያልጠነከረ ህጻናት ጭምር የስደት ሰለባ እየሆኑ እንዳሉ ሆርን ፍሪኩዌንሲ አረጋግጧል::


